አሽራፍ በአንድ ቢሊዮን ብር ያስገነባቸው ፋብሪካዎች ተመረቁ

አሽራፍ የተሰኘው የሱዳን የግብርናና የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ግሩፕ በባህርዳር ከተማ አንድ ቢሊዮን ብር ኢንቨስት አድርጐ ያስገነባቸው ሰባት ፋብሪካዎች ባለፈው ሰኞ ተመረቁ፡፡
የአሽራፍ ግሩፕ ባለቤት አሽራፍ ኤስ. አህመድ ሁሴን በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት፣ ኩባንያዎቹ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ግንባታቸው ሲካሔድ ቢቆይም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሲጓተቱ ቆይተው በተያዘው ዓመት የተጠናቀቁ ሲሆን፣ በዋናነት ከግብርና ጋር የተገናኘ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ የዘይት ማምረቻ፣ የኤክስፖርት ሥጋ ማምረቻ ቄራ፣ የእንስሳት ተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ፣ የበረዶ ማምረቻ ፋብሪካ፣ የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ፣ የውኃና የፍራፍሬ ጭማቂ ማምረቻ እንዲሁም የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ በምረቃው ወቅት በባለስልጣናት የተጐበኙና የአገሪቱን የማምረት አቅም ያሳድጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው፡፡

ከፋብሪካዎቹ መካከል ኤክስፖርት የሚደረግ የሥጋ ምርት የሚቀነባበርበት ቄራ በቀን 600 ዳልጋ ከብቶችን፣ 3000 በግና ፍየሎችን የማረድ አቅም እንዳለው ተጠቅሶለታል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው በዕለቱ ባደረጉትም ንግግር ለቄራው አስተዋጽኦ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ተፈራ እንዳሉት፣ ኩባንያው የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የሥጋ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግ ባሻገር ለእንስሳት ባለሀብቶች፣ አርብቶ አደሮችና ገበሬዎች ተገቢውን የገበያ ዋጋ በመስጠት ሕገወጥ የእንስሳት ንግድን ለመቀነስ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ኩባንያው ወደ ምርት ሲገባም የአገሪቱ የሥጋ ኤክስፖርት በዓመት 60,000 ቶን እንደሚደርስ የገለጹት አቶ ተፈራ፣ ከአምስት ዓመት በኋላም በአማካይ 69,440 ቶን በዓመት ለውጭ ገበያ እየቀረበ ከ250 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በኋላ ከቁም እንስሳት ንግድና ከሥጋ ምርት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን ተናግረው፣ የሥጋ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ የ62 በመቶ እድገት እያስመዘገበ፣ ከአምስት አመት በኋላ 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለሥጋና ለእንስሳት ተዋፅኦ ድጋፍ ለመስጠት እንዲመቸውም የኢትየጵያ የሥጋና የወተት ሀብት ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማቋቋሙን ለኩባንያዎቹ ባለቤት ገልጸውላቸዋል፡፡ በምረቃው ወቅት “ወንድማማቾቹ ኢትዮጵያና ሱዳን” የተሰኘው የጥንት የሱዳን ዘፈንም የምረቃው ማድመቂያ ሆኗል፡፡ አሽራፍ እንዳሉት፣ ሁለቱ ሱዳኖችና ኢትዮጵያ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ለኢኮኖሚው ከሚያበረክቱት ጠቀሜታ ባሻገር ሱዳንና ኢትዮጵያ ያላቸውን ግንኙነት ያጠናክራሉም ብለዋል፡፡ አሽራፍ አክለውም መንግሥት ላደረገላቸው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
እንዲሁም የክልሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ኃላፊ አሽራፍ የተለያዩ ችግሮችን አልፎ ለዚህ መብቃቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

የኩባንያዎቹ ምርቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ይቀርባሉ ያሉት አሽራፍ፣ በዋጋ ረገድም ከውጭ ምርቶች የተሻለ ቅናሽ ኖሯቸው ለገበያ እንደሚቀርቡም ተናግረዋል፡፡ ከምርቶቹ መዳረሻዎች መካከል የጐረቤት አገሮችና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አላማ ተደርገዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ቢጠናቀቁም ምርት የማምረት ሒደቱን በቅርቡ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሰባት አመታት በፊት ባህርዳርን በጐበኙበት ወቅት የከተማይቱን መስህቦች በመመልከት ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት የፈቀዱት አሽራፍ፣ ለሕፃናትና ለእናቶች አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል በነፃ ይገነባል ብለዋል፡፡

በምረቃው ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መኮንን ማንያዘዋል፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣ የባንክ ፕሬዚዳንቶች፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ በኢትዮጵያ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን አምባሳደሮች፣ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር በምረቃው ወቅት ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php?option=com_content&view=article&id=5609:2011-04-06-08-18-33&catid=101:2009-11-13-13-45-28&Itemid=621

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s